Onion-Juice

ፎረፎርን እየቀነሰ የፀጉርን እድገት የሚጭምር ተፈጥሯዊ የሽንኩርት ጁስ

የሽንኩርት ጁስ በቤትሽ ውስጥ በማዘጋጀት ፀጉርሽን ከመርገፍ ከመከላከልሽ በተጨማሪ እድገቱም ከፍ እንዲል ማድረግ ትችያለሽ። ለረጅም ዘመናት ያክል ሴቶች ይሄንን ውህድ ለፀጉራቸው ጤንነት ሲጠቀሙት እንደነበረ ይነገራል።

የሽንኩርት ጁስ ለፀጉር እድገት የሚሰጣቸው ጥቅሞች

  • የሽንኩርት ጁስ በውስጡ “Sulfur” ስለያዘ የደም ዝውውርን ለመጨመር ይሄም የፀጉር ዘለላዎች አስፈላጊ ንጥረነገሮችን እንዲያገኙና እንዲያብቡ ያደርጋል።
  • የሽንኩርት ጁስ “antibacterial and antifungal” ባህሪያት ስላሉት ፎረፎር እንዳይከሰትና ከተከሰተም እንዲቀንስ የማድረግ ሀይል አለው።
  • “Vitamin C” በሽንኩርት ጁስ መገኘቱም ፀጉር እንዳይሰባበር፣ እንዳይበጣጠስ የማድረግ አቅሙ ከፍ እንዲል አስችሎታል።

የሽንኩርት ጁስ አሰራር

ግብዓቶች

  • አንድ ተለቅ ያለ ቀይ ሽንኩርት
  • ቀረፋ
  • የጥብስ ቅጠል (ሮዝሜሪ)

አዘገጃጀት

  • ሽንኩርቱን ከከተፍሽ በኋላ በትንሹ ታጥቢዋለሽ
  • የከተፍሺውን ሽንኩርት ወደ መፍጫ ውስጥ አስገቢ
  • ውሃ በበቂ ሁኔታ ጨምረሽ መፍጨት ጀምሪ
  • የተፈጨውን በማጥለያ/በጨርቅ/በታይት በማጥለል ውሃውን ብቻ አስቀሪ
  • ውሃው ከፍተኛ የሽንኩርት ሽታ ስለሚኖረው ቀረፋ ጨምረሺበት አሳት ላይ ጣጂው።
  • ትክትክ እስኪል አቆይተሽ ሲፈላ አውጪው
  • ሲበርድ ወደምትጠቀሚበት አቃ መገልበጥ
  • አሁንም ሽታ እንዳይኖረው ሌላ ቀረፋ እና የጥብስ ቅጠል አስገቢበት

አጠቃቀም

  • የተዘጋጀውን የሽንኩርት ጁስ የውስጡም የውጪውም የፀጉርሽ ክፍል እስኪዳረስ ድረስ ማሳጅ እያደረግሽ የሽንኩርት ጁሱን መቀባት።
  • ከ30 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት ያክል በ Shower Cap/ፌስታል መሸፈን
  • መታጠብ
  • ሞይስቸራይዝ ለማድረግ ቅባት መጠቀም

አንዳንድ ነጥቦች

  • የሽንኩርት ጁስ ብዙ ፕሮቲን ስለሚኖረው የፀጉር ልስላሴ እጥረት ሊያጋጥምሽ ስለሚችል በሳምንት 1 ወይም 2 ጊዜ ብቻ ብትጠቀሚው ይመረጣል።
  • የሽንኩርት አላርጂክ ካለብሽ መጠቀም የለብሽም።
  • ሴንሴቲቭ ቆዳ ካለሽ ሽንኩርቱን ስትፈጪ ውሃውን ማብዛት አለብሽ።
  • አንዳንድ ሴቶች ላይ ቡግር ሲያባብስ ተስተውሏል።
  • የቆዳ መቆጣት፣ የማሳከክ ስሜት ካጋጠመሽ አቋርጪው።
 

ስለ ሽንኩርት ጁስ ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች

1.የሽንኩርት ጁስ ማንኛውም ሰው መጠቀም ይችላል?

ጥናቱ እንደሚያሳየው አንዳንድ ህክምና የሚሹ ችግሮች እንደ “psoriasis or eczema” ያሉባቸው ሴቶች ከመጠቃማቸው በፊት የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር ያሻል። እንዲሁም የሽንኩርት አላርጂክ የተከሰተባቸው ሴቶች እንዲጠቀሙት አይመከርም።

2. ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ እችላለሁ?

ማቀዝቀዣ / ፍሪጅ ውስጥ በማስገባት መጠቀም ሲያስፈልግ መጠቀምም ይቻላል። ከ 3 እስከ 5 ቀናት ድረስ ባሉት ጊዜያት ብቻ ቢቀመጥ የሚመከረው የሽንኩርት ጁስ ከነዚህ ቀናት ካለፈ ሽታው የመጨመር እድል አለው።

3. ሞይስቸራይዝ ለማድረግ የትኛውን ቅባት ልቀባ?

የሽንኩርት ጁስ ፀጉርን ሊያደርቅ ስለሚችል የሚስማማሽንና ከዚህ በፊት የምትጠቀሚውን የፀጉር ቅባት መጠቀም መቀጠል አለብሽ።

4. የሽንኩርት ጁስ ለሁሉም የፀጉር አይነት ይሆናል?

የሽንኩርት ጁስ ከርዳዳ ፀጉር ያላቸው ሴቶች ሲጠቀሙት እንዳልሰራላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል።

5. የሽንኩርት ጁስ ብቻ ብጠቀም ምን ይፈጠርብኛል?

የበለጠ የፀጉር እድገት እንዲኖር ፀጉርን መንከባከብ ያስፈልጋል። የሽንኩርት ጁስ በዚህ ሳምንት ከተጠቀምሽ በቀጣዩ ደግሞ ሌሎች በሙዝ፣ በሩዝ ፣ አቮካዶ ወዘተ የሚዘጋጁ ሌሎች የፀጉር ማሳደጊያዎችን መጠቀም ለውጡ ቶሎ እንዲጨምር ይረዳል።

6. እርጉዝ ሴት ብትጠቀመው ችግር አለው?

እርግዝና ላይ ያለች ሴት ላይ የሚያመጣው ጉዳት ስለመኖሩ ጥናቶች ሲገልፁ አይስተዋልም። ነገርግን ይሄ ማለት ነፍሰጡር ሴት ለሆነች ሴትም ሴፍ እና መልካም ነው የሚል ጥናት እንደሌለ ልብ ይሏል። ነፍሰጡር ከሆንሽ እና ይሄን የሽንኩርት ጁስ ለመጠቀም ካሰብሽ መጀመሪያ የህክምና ባለሙያዎችን/ዶክተሮችን ማማከር የተሻለ ነው።

Comments are closed.