የሞተ ቆዳን በማንሳት ቆዳን ጥርት እና ፍክት የሚያደርገው ይህን የተፈጥሮ ክሬም በመጠቀም የፊቷን ውበት እንደ ማለዳ ፀሀፍ ፍንትው ብሎ የሚወጣላት ሴት መሆን ትችያለሽ። ተፈጥሯዊ ከመሆኑ ባሻገር ለአዘገጃጀት ቀላል መሆን በብዙ ሴቶች እንዲወደድና እንዲመረጥ አስችሎታል።
ይህ የፊት ክሬም ለፊት ቆዳ የሚሰጣቸው ጥቅሞች
- ሩዝ የሞተ ቆዳን በማስወገድ ቆዳ ጥርት ብሎ እንዲታደስ እና ለስላሳ እንዲሆን የማድረግ አቅም አለው።
- ሙዝ የ”Vitamin C እና E” ምንጭ በመሆኑ ቆዳ ከጉዳት እንዲጠበቅ ያስችለዋል። እንዲሁም በ”Potassium” የበለፀገ በመሆኑ ቆዳ እርጠበት እንዲኖረው ይሄም እንዳይጎዳ ያደርገዋል።
የሩዝና ሙዝ የፊት ክሬም አሰራር
ግብዓቶች
- አንድ የሻይ ብርጭቆ ሩዝ
- መካከለኛ ቁመት ያለው ግማሽ ሙዝ
አዘገጃጀት
- ሩዙን በደንብ አጥበሽ ሙክክ ብሎ እስኪበስል መቀቀል
- ሲበስል ከእሳት ላይ ማውረድ
- ግማሽ ሙዝ ከታትፎ ከበሰለው ሩዝ ጋር አንድ ላይ ክሬም እስኪሆን መፍጨት
አጠቃቀም
- ፊትን በሳሙና/ውሃ ታጥበሽ ማደራረቅ
- የደረቀ ፊት ላይ ይሄንን ክሬም ማሳጅ እያደረግሽ መቀባት
- ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ተቀብቶ መቆየት
- ለብ ባለ ውሃ ፊትሽን መታጠብ
-
በንፁህ እና ለስላሳ ፊትን ማደራረቅ
አንዳንድ ነጥቦች
- ለፊትሽ ቆዳ አላርጂክ ከሆነ መሞከር የለብሽም።
- የምትጠቀሚያቸው ግብዓቶች ያልተበላሹ እና ጤንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጪ።
- ክሬሙን ከተጠቀምሽ በኋላ እንደቆዳሽ አይነት ሞይስቸራይዘር ብትጠቀሚ ይመረጣል።
- ይሄንን ውህድ ለመስራት የሚያስችል ግብዓቶች ከሌለሽ ሌሎች ሴፍስኮዬር ያዘጋጀለሽን ውህዶች መሞከር።
በዚህ ክሬም ጉዳይ ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች
- ለምን ያክል ጊዜ ብቀባው ይመረጣል?
ይሄንን ውህድ በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ሁለቴ መጠቀም ትችያለሽ።
2. እንዳይበላሽብኝ ምን ላድርግ?
የተፈጥሮ ክሬም እንደመሆኑ ወዲያው ሊበላሽ ይችላል። ነገር ግን ፍሪጅ ውስጥ ንፁህ ቦታ ላይ በማስቀመጥ የመበላሻት እድሉን መቀነስ ትችያለሽ። የመጥቆር፣ የሽታና የመሻገት ምልክት ካሳየ ግን መጣል አለብሽ። ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርገው እርግጡ መፍትሄ ለእለት ተእለት የሚሆንሽን ማዘጋጀትና መቀባት ነው።
3. ይሄን የፊት ማስክ ሳዘጋጅ የግድ ሎሚ መጨመር አለብኝ?
የለብሽም! በተለይ በብዙ መጠቀም የፊት መቆጣት ሊያስከትልብሽ ይችላል። ነገርግን ክሬሙን ስታዘጋጂ እና ሲወፍርብሽ በጣም ጥቂት የሎሚ ጭማቂ መጨመር ጥቅም እንድታገኚበትም ያስችላል። ሎሚ በውስጡ “Vitamin C” ስለያዘ ቆዳን ከመጎዳት ከመጠበቁ ባሻገር በቆዳ ላይ የሚፈጠሩ ጥቋቁር ነጠብጣቦች ለማጥፋት ይረዳል። አስታውሺ! ሎሚም ሆነ ሌሎች ግብዓቶች አላርጂክ ካለብሽ መቆጠቡ ይመረጣል።